“ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ” ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ። (መዝሙር 122፣ 1)

እንኳን ወደ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መነሻ ገጽ እንኳን በደህና መጡ። ቤተ ክርስቲያናችን የጸሎት፣ የእምነትና የማኅበረሰብ ማዕከል ናት። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ቅዱስ ትውፊት በመከተል እግዚአብሔርን በፍቅር፣ በሰላምና በመከባበር እናገለግላለን።

ቤተ ክርስቲያናችን በጻድቁ አባታችን ቅዱስ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ስም የተሰየመች ናት። ቅዱሱ በቅድስና ሕይወታቸው፣ በጸሎታቸውና በትሕትናቸው የታወቁ ናቸው።

አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በታኅሣሥ ፳፱ ቀን፣ በ፰፻፳፱ ዓ.ም. ከአባታቸው ስምዖን እና እናታቸው አክለስያ ተወለዱ። ግብፃዊ መነኩሴና ታላቅ ቅዱስ ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ የቤተ ክርስቲያን ቀን መቁጠሪያ በየወሩ በአምስተኛው ቀን መታሰቢያቸው ይከበራል።

አባታቸው እና እናታቸው በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ። ልጅ አልነበራቸውም፤ ለሠላሳ ዓመታትም በሐዘንና በጸሎት ኖሩ። ከዚያም እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ተቀብሎ የተባረከ ልጅ ሰጣቸው። በተወለዱበት ዕለት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ከእናታቸው ክንድ ወርደው በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ሦስት ጊዜ ቆመው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ እንዲህም አሉ፦ «ለአብ ክብር፣ ለወልድ ክብር፣ ለመንፈስ ቅዱስ ክብር ይገባል»

ጻድቁ አባታችን ሕይወታቸውን በሙሉ በበረሃ አሳልፈዋል። በሚያስደንቅ ተጋድሎና ትዕግሥት ለረጅም ዘመናት በዙቋላ ተዘቅዝቀው ሲጸልዩ ኖረዋል፤ በዚህም ለብዙዎች የበረከትና የድኅነት ምክንያት ሆነዋል።

ለመታሰቢያቸው ወርኃዊና ዓመታዊ በዓላትን እናከብራለን። ምንም እንኳን በታኅሣሥ ፳፱ ቀን የተወለዱ ቢሆኑም፣ በዚያ ዕለት የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ስለሚከበር፣ አበው የእርሳቸው በዓል በጥር ፭ ቀን እንዲከበር ሥርዓት ሠርተዋል።

የጻድቁ አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ምልጃ፣ አማላጅነትና በረከታቸው ከሁላችን ጋር ይሁን። አሜን።


Scroll to Top